Saturday, January 3, 2009

ስሪላንካ፤ መንግሥት የዓማጺያኑን ይዞታ ተቆጣጠረ

የስሪላንካ መንግሥት ጦር ሣምንታት ከፈጀ ከባድ ውጊያ በኋላ በደሴቲቱ ሰሜን የምትገኘዋን የታሚል ዓማጺያን መናኸሪያ ኪሊኖቺን መቆጣጠሩ ተነገረ። የአገሪቱ ፕሬዚደንት ማሂንዳ ራጃፓክሤ ይህችው ለአሥር ዓመታት ያህል በታሚል ኤላም ዓማጺያን ቁጥጥር ሥር የቆየችው ከተማ ከመንግሥቱ ጦር ዕጅ መግባቷን በቴሌቪዥን ለሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል። ፕሬዚደንቱ ድሉን ታሪካዊ ሲሉ ዓማጺያኑ ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉም አሳስበዋል። የኪሊኖቺ በመንግሥቱ ወታደሮች መያዝ በአንድ ለዓማጺያኑ ቀረብ ባለ የኢንተርኔት ድህረ-ገጽም ተረጋግጧል። ይህ በዚህ እንዳለ በኪሊኖቺ ድል የተበረታቱት የመንግሥቱ ወታደሮች በአካባቢው የምትገኘውን የወደብ ከተማ ሙላኢቲቩን ለመያዝ እየገፉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። የታሚል ኤላም ዓማጺያን በደሴቲቱ ሰሜን-ምሥራቅ የራሳቸውን ነጻ ግዛት ለማቆም ሲታገሉ 25 ዓመታት አሳልፈዋል። በዚሁ ውዝግብ ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች 70 ሺህ ገደማ ይጠጋሉ።

- DW-RADIO