Thursday, February 19, 2009

ቴዲ አፍሮ ከአምስት ወር በኋላ ይፈታል

ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በመኪና ሰውን ገጭቶ በማምለጥ ወንጀል ክስ ተመስርቶበት በከፍተኛ ፍርድ ቤት የስድስት አመት እስራት እንደተፈረደበት ይታወቃል፡፡

ሆኖም ድምጻዊው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ውሳኔው ተሸሮ በሁለት አመት እስራት ብቻ እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

አውራምባ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙዎች እንዳሉት ‹ያቀረበው የይግባኝ ሰነድ የቀረበበትን ክስ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ነው ሆኖም የስርአቱ አገዛዞች ድምጻዊውን ነጻ ማድረግ ስላልፈለጉና ወንጀለኛ ነው እንዲባል ስለሚፈልጉ ነጻ ከማለት ይልቅ ሁለት አመት ብለው ፈርደውበታል› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቃሊቲ ወህኒ ቤት ኃላፊዎች እንደገለጹልን በወህኒ ቤቱ አሰራር መሰረት አንድ ፍርደኛ ከተፈረበት ፍርድ 1/3ኛውን በአመክሮ ስለሚቀነስለት የሚታሰረው አንድ አመት ከአራት ወር ብቻ ይሆናል ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት እስካሁን ለአስራ አንድ ወራት ያህል በእስር ቤት የቆየው ቴዲ ከአምስት ወር በኋላ ነጻ ይወጣል ተብሎ ይገመታል፡፡

አመክሮ የሚከለከልበት የተለየ ምክንያት አለ ወይ ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የወህኒ ቤት ምንጮች እንደገለጹልን አንድ ታሳሪ የተለየ መጥፎ የዲስፕሊን ችግር ከሌለበት በስተቀር ወይም ለማምለጥ ሙከራ ካላደረገ በቀር የአመክሮ ተጠቃሚ ይሆናል ቴዲ ደግሞ በሁሉም ዘንድ እጅግ የሚወደድ ባህሪና ጨዋ ስነምግባር ያለው ሰው እንደመሆኑ ይህ አይነቱ ክልከላ እርሱን አይመለከትም ብለውናል፡፡