Thursday, February 19, 2009

በይቅርታ የተፈታው ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ወደቃሊቲ እስር ቤት ተመለሰ

(ኢትዮጵያን ሪቪው) - ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ታስረው በምህረት ከተፈቱ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን ከተፈታ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በኋላ ዛሬ ወደቃሊቲ ወረደ፡፡

ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው የነበሩት ጋዜጠኞች በርካታዎቹ አገዛዙ ባደረሰባቸው ወከባና እንግልት ምክንያት አገር ጥለው ሲሰደዱ ከአምስት የማይበልጡቱ ደግሞ በአገር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነኚህ አምስት ጋዜጠኞች የፕሬስ ድርጅት ለማቋቋም ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ‹‹ፍቃድ የምንሰጠው ይቅርታ ፈርመው ለወጡ ጋዜጠኞች ብቻ ነው፡፡ ሲሳይ ሰርካለም እና እስክንድር ግን ፍርድ ቤቱ በነጻ ስላሰናበታቸው አሁንም ህገመንግስቱን ከመናድ ወደኋላ አይሉም፡፡ ይቅርታ የፈረሙቱ ግን ይቅርታቸው እንዳይነሳ ሁሌ እየሰጉ ስለሚሰሩ ይቅርታ የፈረሙበትን ሰነድ ዋናውና ፎቶኮፒ ይዘው ከቀረቡ ለጊዜው እንፈቅዳለን›› በሚል ርካሽና ከፋፋይ ምክንያት ለጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳንና ዳዊት ከበደ ብቻ ተፈቅዶ እያንዳንዳቸው ‹‹ሐራምቤ›› እና ‹‹አውራምባ ታይምስ›› የተሰኙ ጋዜጦችን አቋቁመው በመስራት ላይ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

ሆኖም አገዛዙ በሁለቱም ላይ በርካታ የክስ ዶሴዎችን ሲከምርባቸው እንደቆየ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፈው መስከረም በአስደንጋጭ ሁኔታ የህትመት ዋጋ ሲጨምር ወሰንሰገድ ‹‹ሐራምቤ›› ጋዜጣን መዝጋት ግድ ሆነበት፡፡

የአገዛዙ ግፍና ጭካኔ ግን በዚህ የሚቆም አልሆነም በሚያዚያ 2000 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ እንደ1997ቱ ምርጫ ብዙ ህዝብ አልተሳተፈበትም፡፡ በየቦታው የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች ባዶ እንደነበሩና አስመራጮቹም ባዶውን ኮሮጆ ታቅፈው ሲያዛጉ መዋላቸውን በመዘገቡ ክስ ቀርቦበት ዛሬ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ብር3000(ሦስት ሺህ ብር) ዋስትና እንዲያስይዝ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ሆኖም ጋዜጠኛው ለዚሁ የሚከፍለው ገንዘብ ባለማግኘቱ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡

ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ወደ ቃሊቲ ከማቅናቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አስተያየቱን እንዲሰጥ የኢትዮጵያን ሪቪው ዘጋቢ በልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝቶ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር፡፡ ወሰንሰገድ በሰጠው ምላሽ ‹‹በአስደንጋጭ የህትመት ዋጋ ጭማሪ ምክንያት መስራት ባለመቻሌ ደስ ይበላቸው ብዬ ስራውን ተውኩት የነበረኝ አነስተኛ ገንዘብ ደግሞ ለቀረቡብኝ በርካታ ክሶች ዋስትና አስይዤ ጨረስኩት፡፡ አሁን ግን ምንም የምከፍለው ስለሌለኝ ያለኝ አማራጭ መታሰር ነው›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ከበደም በተመሳሳይ ክስ በነገው ዕለት ከፍተኛ ፍርድቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡