Thursday, January 8, 2009

በጋዜጠኞች ላይ ሞት የጠየቁ አቃቤ ህግ

ከሁለት አመት በፊት ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊውን ስርዓት በሀይል የማፍረስ ወንጀል በሚል በጋዜጠኞችና በቅንጅት አመራሮች ላይ ክስ የመሰረቱና በኋላም በእነኚህ ተከሳሾች ላይ ሞት የጠየቁት አቃቤ ህግ ነጻውን ፕሬስ በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጣቸው፡፡
የኢትየጵያ ብሮድካስት ኤጄንሲ ስራ አስኪያጅ፣በፍትህ ሚኒስቴር ረዳት ጠ/አቃቤ ህግ እንዲሁም የሌሎች ተደራራቢ ሹመቶች ባለቤት የሆኑትና በተለይ አፋኙን የፕሬስ ህግ በማርቀቅ የሚታወቁት አቶ ሽመልስ ከማል አፋኙ ህግ በፓርላማ በጸደቀ ማግስት ማስታወቂያ ሚኒስቴር በአዋጅ መፍረሱ ቢነገርም አፋኙ ህግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣ በኋላ ቀደም ሲል የማስታወቂያ ሚኒስትር ኃላፊነት የነበረው ነጻውን ፕሬስ የመመዝገብና የመቆጣጠር ስልጣን ሰሞኑን በአቶ ሽመልስ ከማል ለሚመራው ብሮድካስቲንግ ኤጄንሲ መሰጠቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለአውራምባ ገለጹ፡፡
እነኚሁ ምንጮች እንደገለጹልን ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በሚገኝበት የማስታወቂያ ሚኒስትር ህንጻ 7ኛ ፎቅ ላይ የነበረው የፕሬስ ፈቃድ መምሪያ ዛሬ ሐሙስ ከሰአት በኋላ ኡራኤል አካባቢ ወደሚገኘው የብሮድካስት ኤጄንሲ ጽ/ቤት የቢሮ እቃዎቹን እያዛወረ ነው ሲሉ ለአውራምባ ታይምስ ገልጸዋል፡፡