Saturday, January 3, 2009

ሚልስ የጋና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኑ

ጋና ውስጥ የተቃዋሚው ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ሸንጎ ዕጩ ጆን-አታ-ሚልስ ባለፈው ሰንበት ተካሂዶ የነበረው ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኑ። ሚልስ ትናንት ቴይን በተሰኘችው ክፍለ-ሐገር በተጠናቀቀው ድምጽ ቆጠራ ከተፎካካሪያቸው ከመንግሥቱ ፓርቲ ዕጩ ከናና-አኩፎ-አዶ ልቀው መገኘታቸውን ጊዜያዊ ውጤት አመልክክቶ ነበር። በዚሁ ውጤት መሠረት ሚልስ 19.566 ድምጽ ሲያገኙ አዶ ያሰባሰቡት ድጋፍ በ 2,035 የተወሰነ ነው። የቴይን ምርጫ ትናንት የተካሄደው በድምጽ መስጫ ቅጾች ክፍፍል ረገድ በተፈጠረ ችግር ባለፈው ሰንበት ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ ነበር። የአስመራጩ ኮሚሢዮን ሊቀ-መንበር ክዋዶ-አፋሪ-ግያሪ አጠቃላዩን ይፋ ውጤት ያስታወቁት ዛሬ ከቀትር በኋላ ላይ ነው። መንግሥታዊው ፓርቲ ተቃዋሚው ወገን ደጋፊዎቹ በሚያመዝኑበት በቮልታ አካባቢ አጭበርብሯል ሲል የቴይንን ምርጫ ለማስቆምና አስመራጩ ኮሚሢዮንም ውጤት እንዳያቀርብ ለማሳገድ ባለፈው ሐሙስ ለፍርድቤት ማመልከቻ አቅርቦ ነበር። ይሁንና ጥረቱ ሳይሰምርለት ቀርቷል።